የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት

ርዕሱ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያን ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል በንጉሠ ነገሥትነት ሲያስተዳድሯት የኖሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያዎቹን የሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥታቸውን አመራር ታሪክ ይህ መጽሐፍ ተንንትኖ አቅርቧል፡፡
በዚህ በሃያ አምስት ዓመታት ዘመነ መንግሥት ውስጥ
1ኛ . የፋሽስት ጣሊያን ወረራ አመጣጥ
2ኛ. የኢትዮጵያን ነጻነት ለማዳን ንጉሠ ነገሥቱ በዤኔቭ የመንግሥታት ማህበር ሸንጎ ላይ ያደረጉት ሙግትና በመጨረሻም ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረገው አሳዛኝ ውሳኔ
3ኛ. ሙሶሊኒ ከሂትለር ጋር ተሰልፎ የአውሮፓን መንግሥት በጦር ሲወጋ ፣ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ አገራችንን ከያዙ በኋላ የጫኑብን የሞግዚት አስተዳደር እንዴት እንደነበረ
4ኛ. ነፃነታችን ከፋሽስት እጅ ከተመለሰ በኋላ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ለመላቀቅ ምን ያህል ድካም እደጠየቀ
5ኛ. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በምሥጡር ወደ ስዌዝ ካናል ተጉዘው ከአሜሪካው መሪ ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ጋር ያደረጉት ንግግር
6ኛ. የኢትዮጵያ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ከተላቀቀች በኋላ በአገር ውስጥ የሁለት ሰዎች (መኮንን ሀብተወልድና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ) የሥልጣን አነሳስና ትብብር ንጉሠ ነገሥቱን ምን ያህል እንደአሳሰባቸው
7ኛ. ከእነዚህ ከሁለቱ ሰዎች መካከል የሥልጣን ኃይላቸው አስጊ ሆኖ የተገመተውን ፣ ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስን በሽረት ከካቢኒያቸው ለማራቅ ንጉሠ ነገሥቱ የወሰዱት እርምጃ
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ስለተገለጸ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን እውነተኛ ታሪክ አንብቦ ለመረዳት ይችላል፡፡
ዘውዴ ረታ

ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ

ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ በሚል ርዕስ እንደ አ.አ. በሐምሌ 1905 ዓ.ም. ለአንባቢዎች የቀረበው መጽሐፍ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ-ነገሥት ሆነው ኢትዮጵያን መምራት ከመጀመራቸው በፊት ደጃዝማች ተፈራ መኰንን ከሐረር ጠቅላይ ገዥነት ተነስተው በምን አኳኋን ባለሙሉ ሥልጣን አልጋወራሽ ለመሆን አንደበቁና ዘውድ እስከጫኑበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን መንግሥት ሲመሩ እንደቆዮ የሚያስረዳ ነው፡፡
ብዚዎች አንባቢዎች አንደሚያውቁት ከአፄ ምኒልክ ሕየወት ፍጻሜ በኋላ በአገራችን በያለበት እየተቀመመ የሚሠራጨው የአፈ ታሪክ ተፈሪ መኮንን የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን የበቁት ልጅ ኢያሱን በኩዴታ ጥለው ንግሥት ዘውዲቱን በሐኪም መርፌ አስገድለው ነው የሚል ነው፡፡
ደራሲው በዚያን ዘመን የተካሄደውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለረዥም ጊዜ ምርምርና ጥናት በማካሄድ
1ኛ. ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን እንዴት እንደወረዱ ፣ ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ዘውድ ለመጫን እንደበቁ
2ኛ. ለመንግሥቱ ሥራ አመራር የራስ መኰንን ልጅ ተፈሪ መኰንን ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴና አልጋ ወራሽ ሆነው እንደተመረጡ
3ኛ. ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ትክክለኛውን ታሪክ ለአንባቢዎች ለማቅረብ ደራሲው ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡

ውሳኔው የአንባቢውች ነው
ዘውዴ ረታ

የኤርትራ ጉዳይ

የኤርትራ ጉዳይ በዚህ ርዕስ ተጽፎ የቀረበው ታሪክ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
1ኛ. አብዛኛው የኤርትራ ሕዝብ ፣ ከባዕድ አገዛዝ ለመላቀቅና ወደ መሠረት አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ኢትዮጵያ ወይ ሞት ብሎ በመታገል ምን ያህል መከራና ፈተና እንደተቀበለ
2ኛ. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋኃድ በአራቱ ኃያላን መንግሥታት ዳንነትና ቀጥሎ በተባበሩት መንግሥታት ሸንጎ ላይ ለብዙ ዓመታት ያደረገው ፋታ የሌለው ሙግት ምን ውጤት እንደሰጡ
3ኛ. በተባበሩ መንግሥታት ሸንጎ ላይ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ፣ ፍርዱ እንዴት እንደተወሰነና፣ ከዚያም ለአሥር ዓመታት የተካሄደው የፌዴሬሽን አስተዳደር በምን መልክ ይሠራበት እንደነበረና በኃላም በምን አኳኋን እንደፈረሰ

እውነተኛውን ታሪክ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች እንዲያውቁት በዝርዝር የተዘጋጀና ከፍ ያለ ጥረት የተደረገበት ነው፡፡
መልካም ንባብ
ዘውዴ ረታ